ኪም ጆንግ ኡን 'ከደቡብ ኮሪያ ጋር የተሻለ ቅርበት' እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ

ኪም ጆንግ ኡን የልዑካን ቡድን አባላቱን ለእራት ሲቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኡን የልዑካን ቡድን አባላቱን ለእራት ሲቀበሉ
ታትሟል

የሰሜን ኮሪያ መሪ የሆኑት ኪም ጆንግ ኡን ከደቡብ ኮሪያ ጋር "የተለየ ቅርበት" እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የሃገራቸው መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ይህ ዘገባ የተሰማው የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ፒዮንግያንግን ከጎበኙ እና እራሱን ከዓለም ማህበረሰብ ከነጠለው መሪ ጋር እራት ከበሉ በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት ኪም ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ከሶል ያገኟቸው የመጀመሪያዎቹ ባለስልጣናት ሆነዋል።

ይህ ጉብኝት የክረምት ኦሎምፒኩን ተከትሎ በፍጥነት እየተሻሻለ የመጣው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አንዱ ማሳያ ነው።

የደቡብ ኮሪያ ኃላፊዎች ስለ ስብሰባው ሁለቱ ሃገራት ወደፊት ለመነጋገር "አመርቂ ስምምነት" ላይ መድረሳቸውን አሳውቀዋል።

ልዑካን ቡድኑ በሚቀጥለው ሳምንት መገባደጃ ላይ ከሰሜን አቻዎቻቸው ጋር ስለነበራቸው ንግግር በዋሽንግተን በመገኘት ለአሜሪካ ባለስልጣናት ገለጻ ያደርጋሉ።

አሜሪካ በበኩሏ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት መሸሻልን "በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነገር ግን ተስፋ ሰጪ" ብላዋለች፤ ነገር ግን ከፒዮንግያንግ ጋር መደበኛ ውይይት ለማድረግ የኒውክሌር ፕሮግራሟን እስካልተወች ድረስ የማይታሰብ ነው ስትል አክላለች።

ኪም ጆንግ ኡን እ.አ.አ. በ2011 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከጥቂት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የተገናኙ ሲሆን የደቡብ ኮሪያ ልዑካን ቡድን በሰሜን ጉብኝት ያደረገው በ2007 ነበር።

ስለዚህ ኪም ከደቡብ ኮሪያ ልዑካን ቡድን ጋር በፈገግታ መጨባበጣቸውና ለእራት መቀመጣቸው ወሳኝ ነገር ነበር።

ከልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል የደህንነት ኃላፊ የሆኑት ሱህ ሁን እና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት ቹንግ እውይ ዮንግ ይገኙበታል።

ዕቅዳቸውም በአንድ ባንዲራ ሥር በመሳተፍ ከክረምት ኦሎምፒኩ በኋላ እየረገበ የመጣውን ውጥረት ማስቀጠል ነው።

ተስፋ ያደረጉትም ለወደፊቱ የሚካሄዱ መደበኛ ውይይቶች መካከል የተጋረጠውን ዲፕሎማሲያዊ ተግዳሮት በአሜረካ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል በመሆን ሰሜን ኮሪያን ለማሳመን እና የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንድታቋርጥ ለማግባባት ነው።

የሰሜን ኮሪያ ዜና ተቋም ኪም ለልዑካን አባላቱ የሞቀ አቀባበል እንዳደረጉላቸውና ግልጽ ውይይት እንዳደረጉ ዘግበዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ወደፊት በሰፊው ለመነጋገር የተላከውን ደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን ኪምም ለደብዳቤው በጎ ምላሽ መስጠታቸው ተዘግቧል።