የሐሙስ ምሽት አለም አቀፍ ዜናዎች፡ ከኢትዮጵያ እስከ ቻይና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባሌ ሮቤ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ እንደሚያደርግ ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, SIMON MAINA

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባሌ ሮቤ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
ታትሟል

ኢትዮጵያ

በ500 ሚሊዮን ብር የተገነባው የባሌ ሮቤ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሀገር ውስጥ የዜና ተቋማት ዘገቡ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሶስት ቀን በረራ የሚጀምር ይሆናል።

ዩጋንዳ

የዩጋንዳ ወታደሮች ራሳቸውን በሩካቤ ከሚተላለፉ በሽታዎች እንዲከላከሉ አዲስ አይነት ኮንዶም ተዘጋጅቶላቸዋል። የወታደራዊ ሀይሉ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሊዮፓርድ ኪያንዳ ለሰራዊታቸው ይህን መልእክት አስተላልፈዋል።

ሶማሊያ

ስራ አጥ የአይቲ ባለሙያ ነኝና ቅጠሩኝ የሚል ጽሁፍ አንግቦ የተዘዋወረ ሶማሊያዊ ስራ አገኘ። የሶማሊያዊው ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ በ48 ሰአት ውስጥ 20 ተቋሞች የእንቅጠርህ ጥያቄ አቅርበውለታል።

ጣልያን

አንድ ጣልያናዊ የባንክ ሀላፊ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከሀብታሞች የባንክ ካዝና ገንዘብ እየሰረቀ በተቸገሩ ሰዎች ሒሳብ ቁጥር ያስገባ ነበር። በስርቆት የተከሰሰው ግለሰቡ የሰረቀውን ገንዘብ ለግል ጥቅሙ ባለማዋሉና ከዚህ ቀደም አጥፍቶ ስለማያውቅ ሳይታሰር ቀርቷል።

ቻይና

ቻይናውያን ስለ ፕሬዘዳንታቸው ዢ ዢፒንግ ምን ያህል እንደሚያውቁ የሚፈተሹበት ጨዋታ እውቅናው እየጨመረ ነው። በቴሌቭዥን የሚተላለፈው ጨዋታው ዋነኛ ግቡ የቻይናን ወጣቶች ማስተማር ነው።

ፔሩ

ፔሩ የቀድሞ ፕሬዘዳንቷን ዳግም ዘብጥያ አወረደች። ፕሬዘዳንቱ በግድያ ክስ ለስምንት ዓመት ከታሳሩ በኋላ በጤና እክል ምክንያት እንዲለቀቁ ቢወሰንም ተጎጂዎች ይግባኝ ስላሉ በድጋሚ እንዲታሰሩ ተወስኗል።

ህንድ

ህንድ ሰባት የሮሂንጋ ሙስሊሞች ወደ ሚያንማር እንዲለሱ ማስገደዷ እያስተቻት ነው። ግለሰቦቹ ወደ ሚያንማር መመለሰቻው ከባድ አደጋ ውስጥ ሊከታቸው ቢችልም ከሀገሯ ከማስወጣት አልታቀበችም።

ከተቀረው አለም

• ባለፉት ስድስት ዓመታት 259 ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ፎቶ ለማንሳት ሲጣጣሩ መሞታቸው ይፋ ሆነ። ከረዣዥም ፎቆችና ከተራራ ሲዘሉ ሰልፊ ለመነሳት የሞከሩ ግለሰቦች ይገኙበታል። ስለዚህም ሰልፊ መነሳት አደገኛ የሆነባቸው ቦታዎች ሊከለሉ ይገባል ተብሏል።

• ሮናልዶ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2009 ላስ ቬጋስ ውስጥ ደፍሮኛል ያለችው መምህርት ጉዳዩን በአደባባይ ለማውጣት የወሲባዊ ትንኮሳን የሚኮንነው 'ሚ ቱ' ንቅናቄ ብርታት እንደሰጣት ተናገረች።