የዛላምበሳ ድንበር ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ይከፈታል ተባለ የሚሉና ሌሎችም ዜናዎች

ኢትዮ-ኤርትራ
የትግራይ ክልል ፕሬዘዳንት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ከፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ስለ ድንበሮች መከፈትና መዘጋት እንዳወሩ ተናግረዋል። የዛላምበሳ መስመር መዘጋት ግንኙነቱን ሕግና ሥርዓት የተከተለ ከማድረግ ውጪ ሌላ ምክንያት የለውም ብለዋል። ፕሬዘዳንቱ በሰጡት መግለጫ የዛላምበሳ ድንበር ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንደሚከፈት አሳውቀዋል።
ጋምቢያ
የጋምቢያ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ሥልጣን ላይ በነበሩበት 22 ዓመታት ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ምስክሮች ቃላቸውን መስጠት ጀምረዋል። ከምስክሮቹ መካከል ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ይገኙበታል።
ግብጽ
ግብጽ የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ከስድስት ወራት በኋላ ታስተናግዳለች። የአፍሪካ ዋንጫን ልታስተናግድ የነበረው ካሜሩን አስፈላጊውን መሰናዶ ባለማድረጓ ካፍ ግብጽ እንድታዘጋጅ ወስኗል።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
አንድ አሜሪካዊ ተመራማሪ ጉግልና ፌስቡክ ስለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምርጫ የተዛባ መረጃ እያሰራጩ ነው ብለዋል። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ባይታወቅም ተቀናቃኙ አካል እንዳሸነፈ የሚጠቁሙ መረጃዎች በጉግልና ፌስቡክ ተነበዋል ተብሏል።
ዛምቢያ
ዛምቢያ አላስፈላጊ የብልት መቆም የሚያስከትል ኃይል ሰጪ መጠጥ ምርት እንዲቆም አድርጋለች። የመጠጡ አምራቾች መጠጡ ውስጥ ጤናማ ያልሆነ ንጥረ ነገር የለም ቢሉም ተጠቃሚዎች ቅሬታ አቅርበዋል።
ደቡብ አፍሪካ
የደቡብ አፍሪካው ኤኤንሲ ፓርቲ 107ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ነፃ ከወጣች በኋላ በብቸኛነት ሥልጣን የጨበጠው ኤኤንሲ ፓርቲ በተለይም ከሙስና ጋር በተያያዘ ስሙ ይብጠለጠላል።
ሰሜን ኮርያ
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ቤጂንግ ገብተዋል። ኪም ወደ ቻይና ያቀኑት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ስለሚያደርጉት ውይይት ለመደራደር ሊሆን ይችላል እየተባለም ነው።
ጀርመን
መራሄተ መንግሥት አንግላ መርክልን ጨምሮ የጀርመን ፖለቲከኞችን የግል መረጃ ከስልካቸው መዝብሮ በትዊተር ይፋ ያደረገው የ20 ዓመት ታዳጊ ነበር ተብሏል። ታዳጊው በፖለቲከኞቹ ንግግር ከመበሳጨት የዘለለ ምክንያት እንዳልነበረው ተመልክቷል።
ጓቲማላ
ጓቲማላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደግፈውን የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሃገሯ ልታስወጣ ነው። ኮሚሽኑ የሃገሪቱን ፕሬዘዳንት እየመረመረ ነበር።













