ፖሊስ ጣቢያ ያቃጠለው ግለሰብ 12 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተከናነበ

የፎቶው ባለመብት, CROW WING COUNTY
ባለፈው ግንቦት በተቀሰቀሰ አመጽ ወቅት የሚኒያፖሊስ ፖሊስ ጣቢያን ያቃጠለው ግለሰብ 12 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተከናነበ፡፡
ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ ያለው የ23 ዓመቱ ዲይላን ሼክስፒር ሮቢንሰን በገንዘብ መቀጮ ብቻ አልታለፈም። የአራት ዓመት እስራትም ይገባሃል ተብሏል፡፡
የሮቢንሰን ጠበቃ ቢሊየነር ካልተሆነ እንዴት ይህ ሁሉ ገንዘብ ይከፈላል በሚል ሁኔታ ደንበኛቸው ቅጣቱን ለመክፈል የሚያስችለው "ተጨባጭ ዕድል የለም" ብለዋል፡፡
ይህን ውሳኔ የሰሙ እና ጥፋተኛ ነን ያሉ ሦስት ግልሰቦችም "እኛስ ምን ይረድብን ይሆን?" እያሉ እየጠበቁ ነው፡፡
ለመሆኑ ፖሊስ ጣቢያው ምን ሆነ?
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ ወደሚኒያፖሊስ ጎዳናዎች ጎረፉ። ምክንያታቸው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረው የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ነበር፡፡
የሚኒያፖሊስ የፖሊስ መኮንን የነበረው ዴሪክ ቻውቪን አሁን ከሥራ ገበታው ተባሯል። ቻውቪን ፍሎይድ አንገት ላይ ተንበርክኮ ከዘጠኝ ደቂቃ በላይ ሲቆይ ተቀርጾ ታይቷል። በድርጊቱም በኋላ ላይ ጥፋተኛ ነህ ተብሏል።
የፍሎይድ ሞት ለሳምንታት የዘለቁ ተቃውሞዎችን ቀሰቀሰ። ከተማዋ በዝርፊያ፣ በእሳት ቃጠሎ እና በሁከት ታመሰች፡፡
ሮቢንሰን ነዋሪነቱ በሚኒሶታዋ ብራይነርድ ነው። ከሚኒያፖሊስ በስተሰሜን 193 ኪሎ ሜትር ብትርቅም ሠልፉን ከመቀላቀል አላገደውም።
ሮቢንሰን የሞሎቶቭ ኮክቴል (ቤት ውስጥ የሚሠራ ተቀጣጣይ ቁስ) አቀጣጥሏል ይላል ዓቃቤ ሕግ። በሚኒያፖሊስ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ላይ የወረወረው እና ሕንፃውን ያቀጣጠለው ግን ሌላ ግለሰብ ነው፡፡
የደህንነት ካሜራዎች ሮቢንሰን ሌላ ሰው የያዘወውን"ተቀጣጣይ ቁስ" ሲለኩስ ይታያል። በኋላም የፎቁ መወጣጫ አጠገብ እሳት ተነስቷል ብለዋል ባለሥልጣናት፡፡
ተጠባባቂው የአሜሪካ ጠበቃ አንደር ፎልክ "ሮቢንሰን ከሕጋዊ ተቃውሞ ይልቅ ሁከትና ጥፋትን መርጧል" ብለዋል፡፡ ቃጠሎው "ሕይወትን አደጋ ላይ ሲጥል በሚኒያፖሊስ ለተስፋፋው ሕገ ወጥነት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡"
ሮቢንሰን የእሳት ቃጠሎ ለመፈፀም በማሴር በአንድ ወንጀል ጥፋተኛነቱን አመነ፡፡ የ27 ዓመቱ ብራይስ ማይክል ዊሊያምስ፣ የ25 ዓመቱ ዴቮን ደ-አንድሬ ተርነር እና የ23 ዓመቱ ብራንደን ሚካኤል ወልፍም በተመሳሳይ ጥፋተኛ ነን ብለዋል፡፡ ሌሎቹ ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነው፡፡
አራቱንም የወከሉት የሮቢንሰን ጠበቃ በአመጹ ከተሳተፉት በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የ23 ዓመቱ ወጣት ያለአግባብ ዒላማ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ጠበቃው ዊሊያም ማውዚ ለኒው ዮርክ ታይምስ "የሺዎችን ቅጣት እሱ እየተቀበለ ነው፡፡ ከሮቢንሰን የበለጠ ያጠፉ ብዙዎች ተለይተው አልታወቁም" ብለዋል፡፡
ቅጣቱ እንዴት ይከፈላል?
አራት ዓመት እስር ያንስሃል የተባለው ሮቢንሰን በ12 ሚሊዮን ዶላር ካሳም እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡
የአሜሪካው የጠበቆች ቢሮ የተወሰነውን ገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ይሰበሰባል። ከደመወዝ፣ ከባንክ ሒሳብ፣ ከጡረታ አበል እና በተለምዶ ዳኞች ከሚወስኑት ወርሃዊ የክፍያ ዕቅድ የሚሰበሰብ ነው፡፡
ሮቢንሰን መክፈል የሚችለው "አነስተኛ መጠን" ብቻ ነው በማለት ጠበቃው ሚውዚ ገልፀው። ሌሎች ሦስቱ ተከሳሾችም የጉዳት ካሣ ክፍያውን በከፊል እንዲከፍሉ ይታዘዛሉ የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
"ከተከሳሾቹ መካከል አንዳቸውም ከፍተኛ ገንዘብ የመክፈል አቅም የላቸውም" ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ጠበቆች ቢሮ ሮቢንሰን የገንዘብ መቀጮውን እንዴት መክፈል ይችላል ለሚለው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ አልሰጡም፡፡
የኤፍቢአይ የሚኒያፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ማይክል ፖል መቀጮውን ተገቢ ብለውታል።
"ተከሳሹ የጋረጠው አደጋ በጣም ከባድ ነበር" ብለዋል ፡፡
ውሳኔው አንድ ሰው የፌደራል ሕጎችን ጥሶ የኃይል እርምጃ ሲወስድ በሕግ እንደሚጠየቅ "ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል" ሲሉ ፖል ተናግረዋል፡፡
አንድ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ከፍተኛ ገንዘብ ሲቀጣ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ እአአ በ2018 አንድ የኦሪገን ዳኛ የ 15 ዓመት ወጣት ከ36 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲከፍል ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡ ወጣቱ ለወራት የዘለቀወን የደን ቃጠሎ መቀስቀሱን በማመኑ ነበር ውሳኔው የተላለፈበት።
የ15 ዓመቱ ወጣት ጠበቃ የገንዘቡን ቅጣት "የማይሆን" እና "ፍጹም ሞኝነት" ብለውታል፡፡
ዳኛው በበኩላቸው በእሳቱ ምክንያት ከሚደርሰው የገንዘብ ጉዳት ያልበለጠ በመሆኑ ውሳኔው "ከወንጀሉ ጋር የተመጣጠነ ነው" ብለዋል፡፡
















