የሄይቲ ፕሬዝደንት በመኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ተገደሉ

ፕሬዝዳንቱና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንቱ በተገደሉበት ጥቃት ባለቤታቸው መቁሰላቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ገልጸዋል
ታትሟል

የሄይቲ ፕሬዝደንት ጆቬለን ሞይስ በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተነገረ።

የካሬቢያኗ አገር መሪ በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸውን ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ክላውድ ጆሴፍ አስታውቀዋል።

አሶሲዬትድ ፕሬስ በበኩሉ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በፕሬዝደንቱ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ፕሬዝደንቱ መገደላቸውን እና ቀደማዊ እመቤቷ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ዘግቧል።

ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚንስትሩ በፕሬዝደንቱ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት፤ "ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር" በማለት የተቹት ሲሆን፤ የአገሪቱ ፖሊስ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጉዳዩን በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል ብለዋል።

ይህ የፕሬዝደንቱ ግድያ የተሰማው የካሬቢያኗ አገር ሄይቲ ከመቼውም በላይ በፖለቲካ ልዩነት ሕዝቦቿ በተከፋፈሉበት ወቅት እና በኢኮኖሚ ድቀት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ተከስቶ በሚገኝበት ወቅት ነው።

የ53 ዓመቱ ጆቫኔል ሞይስ እአአ ከ2017 ጀምሮ ሄይቲን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት አስተዳደራቸው በብልሹ አሥራር እና ሙስና ሲወቀስ ቆይቷል። ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ተቃውሞንም ሲያስተናግዱ ቆይተዋል።