ብሊንከን በሄይቲ የታገቱ ዜጎችን ለማስለቀቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን አሉ

ሄይቲ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በሄይቲ የታገቱ አሜሪካውያንን ለማስለቀቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘገበ።

ብሊንከን ይህን ያሉት 17 ሰዎችን አግቶ የወሰደው ቡድን ላገታቸው ሚስዮናዊያን 17 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈለው ከጠየቀ በኋላ ነው።

ቅዳሜ ዕለት ከአሜሪካ እና ከከናዳ የተወጣጡ የሚስዮናዊያንን ቡድን በሄይቲ ያገተው ቡድን ለእያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ዶላር መጠየቁን የሄይቲ የፍትህ ሚኒስትር ለዎል ስትሪት ጆርናል አስታውቆ ነበር።

ይህ ቡድን ለገንዘብ ሲል የሰዎችን በማገት ይታወቃል።

400 ማዞዎ የተባለው ቡድን በሚያዝያ ወር የካቶሊክ ቀሳውስትን አግቶ ይዞ ነበር።

ቀሳውስቱ የተለቀቁ ሲሆን ቡድኑ ሰዎቹን የለቀቀው ገንዘብ ከተከፈለው በኋላ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

ታፍነው የተወሰዱት እነማን ናቸው?

ታፍነው ከተወሰዱት አንዱ ካናዳዊ ሲሆኑ ሌሎቹ በሙሉ የአሜሪካ ዜጎች ናቸው።

ከተያዙት መካከል አምስት ወንዶች፣ ሰባት ሴቶች እና አምስት ልጆች ይገኙበታል። የትንሹ እድሜው ሁለት ዓመት እንደሆነ ተጠቅሷል።

ታጋቾቹ የሄይቲ ልጆች መጠለያ፣ ምግብ እና ልብስ የሚያቀርብ መቀመጫውን በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ያደረገ ክርስቲያን ኤይድ ሚኒስትሪ ለተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ሚስዮናዊ ድርጅት የሚሠሩ ናቸው።

ሚስዮናውያኑ ወላጅ አልባ ሕጻናትን ጉብኝተው ሲመለሱ ከዋና ከተማዋ ፖርተ ፕሪንስ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው ጋንቴር ከተማ የሚጓዙበት አውቶቡስ በወንበዴ ቡድኑ አባላት ተይዟል።

400 የማዞዎ ቡድን ራሱን ለመደገፍ ከሚጠቀምባቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ተሽከርካሪዎችን እና መንገደኞችን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ ነው።

ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው ከታጋቾች መካከል አንዱ የድረሱልን ጥሪ በዋትስአፕ ማስተላለፉን ገልጿል።

ዋይት ኃውስ ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና ኤፍቢአይ በጉዳዩ ዙሪያ የሄይቲ ባለሥልጣናትን እየረዱ ነው።

የሄይቲ የክርስቲያን ኤይድ ሚንስትሪ የቀድሞ ዳይሬክተር ለሲኤንኤን እንደገለፁት አጋቾቹ ከድርጅቱ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል።

የሪፐብሊካን የኮንግረስ አባል አዳም ኪንዚንገር ለሲኤንኤን አሜሪካ ከአጋቾቹ ጋር መደራደር ያለባት ቢሆንም ክፍያ ግን መፈጸም የለበትም ብለዋል።

"የት እንዳሉ መከታተል እና ገንዘብ ሳይከፈል ድርድር ማድረግ ይቻል እንደሆነ ማየት አለብን። ወይም በወታደራዊ ወይም በፖሊስ በኩል ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ ያድርጉ" ብለዋል።

በሄይቲ አገታ ምን ያህል ተስፋፍቷል?

ሄይቲ በዓለም ላይ ከፍተኛ እገታ ከሚደረገባቸው አገራት አንዷ ናት።

የአከባቢው የሲቪል ማህበረሰብ ቡድን እንደገለጸው በዚህ በ 2021 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ከ600 በላይ አገታዎች ተመዝግበዋል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ 231 እገታዎች ናቸው የተመዘገቡት።

አጋቾች ከሁሉም የኑሮ ደረጃ የመጡ የአገሪቱን እና የውጭ ዜጎችን እያፈኑ ነው በማለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታውቃ ነበር።

ሐምሌ ወር ላይ ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞሴ መገደላቸውን ተከትሎ ተፎካካሪ ቡድኖች ስልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ፍትጊያና የፖሊስ ኃይል በመዳከሙ ሃገሪቱ የበለጠ ትርምስ ውስጥ ወድቃለች።